News and EventsShow More
ኮሌጁ በቀጣይ 3 እና 4 ወራት ውስጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን የISO ሰርተፍኬት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
ደብረብርሃን፣ጥቅምት 22/2017(ደብኮ):- የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቀጣይ 3 እና 4 ወራት ውስጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን የISO 9001/2015 ሰርተፍኬት ለማግኘት ለመምህራን እና ሠራተኞች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ባሻዬ በየነ እንደገለጹት ኮሌጃቸው አዳዲስ እሳቤዎችን መነሻ በማድረግ ለኢንተርፕራይዞች፣ ለደብረብርሃንና ለሰሜን ሸዋ አካባቢዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ለተሽከርካሪዎች የቦሎ ምርመራ ፣ለሾፌሮች ስልጠና በመስጠት በአንድ በኩል ለህብረተሰቡ ተስማሚ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ በሌላ በኩል ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ ተቋማቸው እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለይም በክልሉ ከፍተኛ ሰልጣኝ ተቀብሎ በጥራት በማሰልጠን ተወዳዳሪነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል።

የኮሌጁን ተወዳዳሪነት በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ በISO 9001/2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ዙሪያ 3 መቶ ለሚሆኑ መምህራን እና ሠራተኞች ስልጠና እየሰጡ መሆኑን አቶ ባሻዬ አመልክተዋል።

ስልጠናው የዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት ያሟላ እንዲሆን በISO የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እና በISO ኦዲቲንግ ዙሪያ ለ5 አሰልጣኝ መምህራን በኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለስልጣን ስልጠና መውሰዳቸውን አስረድተዋል።

ኮሌጃቸው ከስልጠና በኃላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ እንደሚገባና በቀጣይ 3 እና 4 ወራት ውስጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን የISO ሰርተፍኬት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን አስታወቀዋል።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተቀባይነት ያላቸው ሰልጣኞችን ለማፍራት የኮሌጁ የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራን እና ሠራተኞች ከፍተኛ መነሳሳት ማሳየታቸውን እና መግባባት ላይ መድረሳቸውን ዲኑ አብራርተዋል።

የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የጥራት ማረጋገጥ ኃላፊ ኢንስትራክተር ተስፋዬ አያሌው በበኩላቸው እንደገለጹት ISO ብዙ ጊዜ ለትልልቅ ኩባንያ እና ለምርት ተቋም ብቻ ሳይሆን ከትንሽ እስከ ትልቅ ተቋም የሚያገለግል የስራ አመራር ስርዓት የሚዘረጋ መሆኑን አመልክተዋል።

ተቋማቸው ISO 9001/2015 ወይም የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ISO ስራ በቀላሉ እንዲሰራ የሚያደርግ ፣ምርታማነትን የሚጨምር፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የደንበኛ እርካታን የሚያሳድግ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚሁ መሠረት ተቋማቸው ከዚህ በፊት የሚታወቅበትን አሻሽሎ ISOን በመተግበር የሰልጣኞችን ፣የኢንተርፕራይዞችን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ እና የመንግስትን እርካታ በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰራ አመልክተዋል።
Date Posted: 2024-11-04 16:48:29

4447
Views