News and Events | Show More |
የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የደብረብርሃን ከተማ እና የሰሜን ሸዋ የፖሊ ቴክኒክ እና የኮሌጆች የ4 ወራት አፈፃጸም ግምገማ እያካሄደ ነው |
«በበጀት ዓመቱ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው» - አማረ አለሙ ደብረብርሃን ፡ ኅዳር 4/2017ዓ.ም የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የደብረብርሃን ከተማ እና የሰሜን ሸዋ የፖሊ ቴክኒክ እና የኮሌጆች የ4 ወራት አፈፃጸም ግምገማ እያካሄደ ነው የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አማረ አለሙ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የመድረኩ ዓላማ የሩብ ዓመቱን አፈፃጸም በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል። ኮሌጆች በተሰጣቸው የ100 ቀናት ዕቅድ መሠረት አፈፃጸሙን በመገምገም ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና እጥረቶችን ለማስተካከል የውይይት መድረኩ መመቻቸቱን አንስተዋል። በተለይም ከመደበኛ ስልጠና በዘለለ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና በመስጠት ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን እንዲለውጡ ኮሌጆች እና የዘርፉ ተዋናዮች ብዙ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። በመንግስት ድጋፍ ተደርጎላቸው ዘላቂ እና ወደ መካከለኛ ባለሃብት የሚሸጋገሩ ወጣቶችንና ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራት አንድ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በዲጅታላይዜሽን ዘርፍ ኮሌጆች የማስፋፋት ስራዎችን እንዴት እየተገበሩ እንደሆነና በሌሎችም ተግባራት ላይ ውይይቱ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በ2017 ዓ.ም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎቸ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በተያያዘም በመደበኛ ትምህርትና ስልጠና 198ሺ ፣ በኢንተርፕራይዝ ስልጠና 958ሺ፣ በቴክኒካል ስልጠና 456ሺ ወጣቶችን ለማሰልጠን መታቀዱን አመልክተዋል። የደብረብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ባሻየ በየነ የኮሌጃቸውን ዕቅድ አፈፃጸም አቅርበዋል። በግምገማ መድረኩ የደብረ ብርሃን ከተማ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ የስራና ስልጠና የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። |
Date Posted: 2024-11-15 05:06:44 |