News and EventsShow More
4ኛው ሀገርአቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የጥናትና ምርምር ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው።
የኢፌዲሪ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 4ኛው ሀገርአቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የጥናትና ምርምር ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን መካሄድ ጀመሯል።
ውድድሩን በይፋ ያስጀመሩት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የዘመኑ ዐርበኝነት ድህነትና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
የክህሎት ልማት ለሀገራችን ዕድገት እና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን በማመን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሰራናቸው ስራዎች በፈጠራ የበሰሉ ብሩህ አዕምሮዎችን፣ የተፍታቱ እጆችን፣ በክህሎታቸው የበቁ ዜጎችን ለማፍራት አስችለዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወራሪ ጠላትን መክተው ሉዓላዊነቷን ያስጠበቁ ጀግኖች ዐርበኞች እንደነበሯት ሁሉ ፤ ዛሬ ደግሞ የሙያንና የክህሎትን አቅም በመጠቀም ግብርናችንን የሚያዘምኑ፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት ወሳኝ መነሻ የሆኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ፣ ዲጂታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ ብቁ ሙያተኞች አሏት በማለት ተናንረዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ውድድሩ ከውድድር ባለፈ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የሚያደርግበት ሥርዓት ያበጀ ነው ብለዋል።
ይህ ውድድር የዘመናችንን አድዋ መሐንዲሶችን የምናገኝበትና የምናፈራበት ፕሮግራም ነው ሲሉም ገልጽታል።
ከውድድሩ በኋላ የተመረጡ የፈጠራ ውጤቶች ይበልጥ ዳብረው ወደ ብዝሀ ምርት የሚገቡበት ሁኔታ እንደተመቻቸ የገለጹት ክብርት ሚኒስትሯ
በ3ኛው አገርአቀፍ ውድድር የተገኙ የፈጠራ ውጤቶች የዳበሩበት እና በርካታ ቴክኖሎጂስቶችን ማፍራት የተቻለበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ውድድሩ ከ250 በላይ ዜጎችን የሚያሳትፍ ሲሆን በውድድር አይነትና ጥራት ካለፉት ውድድሮች ተሻሽሎ መቅረቡን ክብርት ሚኒስትር ጨምረው ገልጸዋል።
አራተኛውን የኢትዮ-ክህሎት ውድድር ልዩ የሚያደርገው በ22 ክህሎቶች ውድድር የሚደረግበትና ከ70 በላይ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ የቀረቡበት መሆኑን ክብርት ሚኒስትር ገልጸዋል።
‘’ብሩህ አእምሮዎች፣ ለስራ የበቁ ዜጎች’’ በሚል መሪ ቃል ውድድሩ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ግቢ እየተደረገ ይገኛል።
Date Posted: 2025-05-06 06:41:55

15177
Views